በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ውጤታማ አመራር የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ውጤታማ አመራር የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ውጤታማ አመራር የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ስኬታማ ስራዎች እንዲከናወኑ ማስቻሉን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የ2018 ሩብ በጀት ዓመት በፓርቲ እና በህዝብ ንቅናቄ ስራዎች ላይ ያተኮረ የግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የፓርቲው አመራሮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በየዘርፉ ያለው አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፓርቲው ተግባራዊ ያደረገው ውጤታማ አመራር ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬታማ ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል።
ትልልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ጠቅሰው፤ በሁሉም መስክ አበረታች ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
መደመርን ማዕከል በማድረግ የፓርቲው፣ የህዝቡና የግሉን ዘርፍ በማቀናጀት ያሉ አገራዊ አቅሞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጉ ለስኬቱ መገኘት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
ገቢር ነበብ አካሄድን በመከተል በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን እና ዕድሎችን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ባህል እየዳበረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በዛሬው የግምገማ መድረክ በጋራ የታቀዱ ጉዳዮችን አፈጻጸም መገምገም እንዲሁም በቀጣይ ርብርብ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ለይቶ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
የግምገማ መድረኩ በክልሎች መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ የአፈጻጸም ወጥነት እንዲኖር ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።