ቀጥታ፡

ስታርት አፕ ለስራ እድል ፈጠራ እድገት የሚኖረውን አቅም ለመጠቀም ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ነው 

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፡-ስታርት አፕ ለስራ እድል ፈጠራ እድገት የሚኖረውን አቅም ለመጠቀም ምቹ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለፁ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የስታርት አፕ ስነ ምኅዳሩን ማስፋት የሚያስችል የክህሎት ልማት እና አዳዲስ የስራ  ዕድል ፈጠራን የሚያበረታቱ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች የሚወዳደሩበት "ብሩህ ኢትዮጵያ" የክህሎት ውድድር ሀገራዊ ልማትን የሚያሳልጥና ስታርት አፖችን ማፍራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 350  የፈጠራ ሀሳብ ላላቸው ዜጎች እውቅና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚኖረውን ፋይዳ አሟጦ ለመጠቀም አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብ ላላቸው ስታርት አፖች የመስሪያ ቦታ፣ የፋይናንስ፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡


 

የዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ስታርት አፕ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ስታርት አፖች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስታርት አፕ ዘርፍ ኃላፊ ሙልጌታ ውቤ በበኩላቸው፤የወጣቶች የስራ ፈጠራ ዝንባሌ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡


 

መንግስት የወጣቶችን ተሳተፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የስታርት አፕ አዋጅ በማጽደቅ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡

የፈጠራ ሀሳቦች ስታርት አፕ መሆናቸው በህግ ተለይቶ ምዝገባና ስያሜ ከተሰጠ በኋላ አስፈላጊው የፋይናንስና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አዋጁን ገቢራዊ ለማድረግ ሀገር አቀፍ የስታርት አፕ ፖርታል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ የማስፈጸሚያ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም