የታሪካዊ ባላንጣዎቹ ፍልሚያ በአንፊልድ ሮድ - ኢዜአ አማርኛ
የታሪካዊ ባላንጣዎቹ ፍልሚያ በአንፊልድ ሮድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሊቨርፑል እና ማንችስተር ዩናይትድ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሊቨርፑል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ግቦችን አስተናግዷል።
ቀያዮቹ በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ በሊጉ ባካሄዳቸው 7 ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 3 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
ቡድኑ በጨዋታዎቹ 9 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበት በ10 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 219 ጊዜ ተገናኝተው ማንችስተር ዩናይትድ 85 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሊቨርፑል 73 ጊዜ በማሸነፍ 61 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ክለቦች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጓቸው 62 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 28 ጊዜ ሲያሸንፍ ሊቨርፑል 19 ጊዜ አሸንፎ 15 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በአንጻሩ ማንችስተር ዩናይትድ በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
ለ131 ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ያላቸው ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ የሊጉን ዋንጫ 20 ጊዜ በማንሳት ስኬታማ ክለቦች ናቸው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል የዛሬው ጨዋታ ከሁለት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ነው። ቡድኑ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ያደርጋል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ ካሸነፈ በሩበን አሞሪም ስር በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድል ያስመዘግባል።
የ40 ዓመቱ እንግሊዛዊ ማይክል ኦሊቫር ወሳኙን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው የሊጉ መርሃ ግብር ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከአስቶንቪላ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።