የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 51ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ዛሬ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 51ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ዛሬ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
ቡድኖቹ በሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለ51ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም 50 ጊዜ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 9 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 20 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በ50ዎቹ ጨዋታዎች በድምሩ 97 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 63 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 34 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች በ2017 ዓ.ም የውድድር ዓመት ባደረጓቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና በ60 ነጥብ ሁለተኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ49 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ አንድ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
የሁለቱ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ መቻል ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 12 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።