ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ስብራቶችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተንትኖ አስቀምጧል - አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የተጠራቀሙ ችግሮችን እና ስብራቶችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተንትኖ አስቀምጧል አሉ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተፃፈው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዙሪያ በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ የኢፌዲሪ ኤምባሲ እና በሪያድ የኢትዮጰ‍ያ ኮሙኒቲ ማህበር በጋራ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት ተካሄደ።


 

በፕሮግራሙ ላይ በሳኡዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) መጽሐፉ እያንዳንዳችንን እንደ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና እንደ ሀገር የሚመለከቱን ጉዳዮች የተካተቱበት ስለሆነ ሁላችንም ሊኖረንና ልናነበው የሚገባ ነው ብለዋል።

በተለይም በሀገር ደረጃ የተጠራቀሙ ችግሮችን እና ስብራቶችን ነቅሶ ያወጣ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተንትኖ ያስቀመጠ በመሆኑ ሁላችንም በጥልቀት ልናውቀውና ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ሃሳቦች የወደፊት ተስፋዎች ብቻ ሳይሆኑ ባለፉት የለውጥ አመታት ተተግብረው ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ የጀመሩ እና ሀገራችንን ወደተሻለ ብልጽግና ለማሸጋገር ተስፋን የፈነጠቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይህንንም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከተማውንና ገጠሩን የአገራችንን አካባቢዎች በፍጥነት እየቀየሩ ያሉ ኢኒሼቲቮች ተጀምረው በአጭር ግዜ ውስጥ መጠናቀቅ መጀመራቸው የሃሳቦቹን ተግባራዊነት እና ገቢራዊነት የሚያሳዩ ናቸውም ነው ያሉት።

አምባሳደሩ የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ ለሀገር ልማት እና ለበጎ አድራጎት ስራዎች የሚውል መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ መፅሐፉ በራሱ እንደ አንድ ራሱን የቻለ ሀገራዊ ፕሮጀክት እንዲታይ የሚያደርገው ነው ሲሉ አንስተዋል።

የሪያድ ኮሙኒቲ በተለያዩ ወቅቶች ለሚቀርቡ የሀገር ልማት እና በጎአድራጎት አገራዊ ጥሪዎች ቀናኢነቱን ደጋግሞ እንዳስመሰከረው ሁሉ ይህንን መፅሐፍ ቀድሞ በመውሰድ ግንባር ቀደም ተሳታፊነቱን በማረጋገጡ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።


 

በውይይቱ ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት በሪያድ የኢትዮጵያውያን ኮሙኒቲ ሊቀመንበር አቶ ሱለይማን ሙሃመድ በበኩላቸው ይህ መጽሐፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት መገኘት እንዳለበት ተናግረዋል።

በመድረኩም የመጽሐፍ ዳሰሳ ውይይት መካሄዱን የኤፍ ኤም ሲ ዘገባ ያመላክታል።

በመጨረሻም ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረክቱ አካላት የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ሽልማት መርኃ ግብር ተካሂዶ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

በፕሮግራሙ ላይ አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድርን ጨምሮ ፣ አምባሳደር አወል ወግሪስ ሙሃመድ፣ ዲፕሎማቶች፣ የኮሙኒቲ ሊቀመንበር፣ የተለያዩ የኮሙኒቲ አደረጃጀቶች ፣ መምህራን እና የዳያስፖራ ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም