ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አሰብና ቀይ ባሕርን ያጣችበት ሂደት በአሻጥር የተቀነባበረ እንጅ ሕጋዊ መሠረት የለውም

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ አሰብንና ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት እንደሌለው የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ገለጹ።

የቀይ ባሕር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በመስመሩ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደነበረችና በወቅቱም ከዓለም ትላልቅ ስልጣኔዎች እና ንግድ ጋር ከፍተኛ ትስስር እንደነበራት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሴነሳ ደምሴ ገልጸዋል።

ኤርትራ ተገንጥላ ሀገር ስትሆን በተወሳሰበ ተንኮልና አሻጥር ኢትዮጵያ ደካማ እንድትሆን በሚፈልጉ ኃይሎች ጭምር ጫና ተደርጎባት የባሕር በሯን እንድታጣ መደረጉንም አውስተዋል።

ሆኖም የ30 ዓመታት ታሪክ ከዚያ በፊት ከነበሩት አያሌ ዓመታት ባለቤትነት እንደማይበልጥ ገልጸዋል።

እንዲሁም ከነበረው ትስስር አንጻር ስለ አሰብና ቀይ ባሕር ስናነሳ ከኢትዮጵያ ነጥለን ማንሳት አይቻልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ቅርብ መሆኗ እየታወቀ፤ ሌሎች ሀገራት በርካታ ማይሎችን ተጉዘው ቀይ ባሕርን እንዳሻቸው ሲጠቀሙ፣ ጭራሽ እንደከልካይ፣ ፈቃጅ እና ተቆጣጣሪ ሲያደርጋቸው እየታዘብን ነው ብለዋል።

እዚህ አካባቢ ያሉ ባለድርሻ አካላት ነን ባዮች ከሩቅ ሀገር መጥተው እንደፈለጉ የሚሆኑትን ሳይጠይቁ ኢትዮጵያ ልጠቀም ስትል ግን እንዳይሳካ ለማድረግ ምን ያህል አሻጥርና ተንኮል እንደሚተበትቡ መታዘባቸውንም አንስተዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሰብን እና ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አሥረድተዋል።

ለዚህም በምክንያትነት ከሚነሱት መካከል፤በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት መሆኑ ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ይሁንታ መንግሥትነትን ያላገኘ አካል ይህን የማድረግ ሥልጣንም ሆነ ኃላፊነት የለውም ብለዋል።

ወደቡን አሳልፎ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አለመሆኑ ደግሞ በዓለም አቀፍ ሕግና ደንቦች መነጽር ሲታይ ወደቡን ማጣቷ ትክክል እንዳይሆን ያደርገዋል ነው ያሉት።

ስለዚህ መንግሥት አሁን ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚገባት መጠየቁ ትክክለኛ ነው፤እንዲያውም ከለውጡ በፊት በነበሩት መንግሥታት መነሳት እና መመለስ የነበረበት ነው ሲሉ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም