የጥርስ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ምን ይደረግ? - ኢዜአ አማርኛ
የጥርስ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ምን ይደረግ?

የጥርስ ህመም መንስዔዎችና መከላከል የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአፍና የጥርስ ሐኪም እና መምህርት ዶክተር ካሰች አያሌው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የጥርስ ህመም መንስዔ ምንድን ነው?
ለጥርስና ተያያዥ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ካሰች፤ ከእነዚህም መካከል፡-
የጥርስ ባክቴሪያ፤
የተመጣጠነ አመጋገብ አለመኖር (ጣፋጭ ምግቦችን ማዘውተር)፤
በትጋት የአፍ ንጽህናን አለመጠበቅ እንዲሁም
ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም እና አደጋዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ጭንቀት፣ የሆርሞን ተጽዕኖ፣ የውስጥ የጤና ሁኔታ መታወክ (ለምሳሌ፡- የልብ፣ የኩላሊት፣ የላይኛው መተንፈሻ አካል እና የስኳር ህመም)፣ በዘር ሐረግ የመተላለፍ ሁኔታ፣ በቂ ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙና አለመጠቀምና የብሩሽ ንጽህና መጓደልን በመንስዔነት ዘርዝረዋል።
የጥርስ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ምን ይደረግ?
የአፍ እና የጥርስ ንጽህናን መጠበቅ (ከቁርስና ከእራት በኋላ በቀን ሁለት ጊዜ ከ3 እስከ 5 ደቂቃ ጥርስን መቦረሽ)፤
አመጋገብን ማስተካከል (ጣፋጭ ምግቦችን አለማዘውተር፤ ለጥርስ ጤና ጠቃሚ ምግቦችን መመገብ)፤
ቢያንስ በ6 ወር አንድ ጊዜ የአፍ ውስጥ ጤና ምርመራ ማድረግ፤
በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚጎዱ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ካሉ አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ማድረግ ለጥርስ ህመም የመጋለጥ ዕድልን እንደሚቀንሱ አስገንዝበዋል።
የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ያድርጉ?
የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ያለውን የህመም ሁኔታ በምርመራ አረጋግጠው የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
እንዲሁም ህመሙ እንዳይባባስ የአመጋገብ ሁኔታን ማስተካከል ብሎም ጨው የተጨመረበት ለብ ያለ ውኃን በመጠቀም ከምግብ በኋላ አፍን መጉመጥመጥ እንደሚመከር ጠቁመዋል።