የወጪ ምርት መጠን፣መዳረሻ እና ጥራትን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወጪ ምርት መጠን፣መዳረሻ እና ጥራትን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፡- ለውጪ ገበያ የሚላኩ ምርቶች መጠን፣የገበያ መዳረሻዎች ማስፋት እና ጥራትን ማስጠበቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል አለ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ማምረት እያስቻለ መሆኑን በሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ በቀለ ከተማ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ በትኩረት እንዲሠራና በቂ አቅርቦት እንዲኖር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ለወጪ ንግድ የተዘጋጀ ምርት ለኮንትሮባንድ እንዳይጋለጥ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከመዳረሻ ሀገራት ማስፋፋት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የነበሩ የመዳረሻ ሀገራት የሚወስዱትን ምርት መጠን እንዲያሳድጉ እና ተጨማሪ አዳዲስ ሀገራትም ወደ መዳረሻነት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለዚህም በዓለም አቀፍ የንግድና ዐውደ-ርዕዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ምርቶችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥ የወጪ ምርቶች ላይ የሚሠሩትን የማበረታታት እና ከተለያዩ ሀገራት ጋርም የሁለትዮሽ ውይይትና ስምምነት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ለአብነትም ባለፉት ሦስት ወራት ከ18 ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የወጪ ንግድ ስምምነት አድርገናል ብለዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የወጪ ምርቶችን እና መዳረሻዎችን እንደሚያሰፋ ጠቁመው፤ቻድና ዑጋንዳም የእኛን ምርቶች እንደ አዲስ መውሰድ ጀምረዋል ነው ያሉት።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆንም የመዳረሻ ሀገራትን እንደሚያበዛ ገልጸው፤ አባል ለመሆን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምርቶች ጥራት አንደራደርም ያሉት አቶ በቀለ ከዚህ አኳያ በጥራት መንደር ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው፤የኢትዮጵያ ምርቶች በውጭ ሀገራት ተመራጭ እየሆኑ ያሉትም ለጥራት ባለን የላቀ ትጋት ነው ብለዋል።