ቀጥታ፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ትላልቅ የሪፎርም አጀንዳዎች ለመደገፍ ቁርጠኝነቱን አረጋገጠ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ትላልቅ የሪፎርም አጀንዳዎች ለመደገፍ ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከአዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰዲ ኦልድ ታህ ጋር በኢትዮጵያ እና በባንኩ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይቱ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2025 እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ አመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ሲሆን የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ተመላክቷል።

በውይይቱ አቶ አህመድ ሽዴ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት አካባቢን ምቹ ለማድረግ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግና የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ አቅም ለማጠናከር ያለመ የሪፎርም ስራዎች አስመልክተው ለፕሬዝዳንቱ ገለፃ አድርገዋል።

በአዲሱ ግዙፍ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ አዳዲስ መረጃዎችን ያካተተ ውይይት ያካሄዱ መካሄዱና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ አቅራቢ በመሆን ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስረድተዋል።

አቶ አህመድ ዶክተር ሲዲ ታህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልክት ያስተላለፉ ሲሆን በአመራር ሰጭነታቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

የግሩፑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲዲ ኦልድ ታህ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ትላልቅ የሪፎርም አጀንዳዎችን አፈፃፀም አድንቀው፣ ባንኩ የሀገሪቱን ትልቅ የለውጥ አጀንዳ በበጀት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በግብርና እና በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ትስስርን በማጠናከር የቀጣናዊ ትስስርና ውህደት እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም