ቀጥታ፡

የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ነው - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት አርሶ አደሩ ዓመቱን በሙሉ በማምረት የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥና የገቢ አቅሙ እንዲጨምር የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ የሚገኘውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ መርቀዋል።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) በምርቃቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ለዓመታት ሲባክን የነበረው የወልመል ወንዝ ዛሬ ተመርቆ የአካባቢውን ማህበረሰብ በልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ 20ሺህ የሚሆኑ አባውራዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።


 

አራት ዓመታትን የፈጀው የፕሮጀክቱ ግንባታ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተረገበትም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከግንባታው ጅማሮ እስከ ፍጻሜው ላደረጉት ያልተገደበ ድጋፍና ላሳዩት በሳል አመራርም ሚኒስትሩ አመስግነዋል።

አጠቃላይ ፕሮጀክቱ የውሃ መቀልበሻ ውቅር 33 ኪሎ ሜትር ውሃ ማስቀየሻ የመጀመሪያ ቦይ(ፕራይመሪ ካናል)፣ 47 ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ቦይ(ሰከንደሪ ካናል) እና 64 ኪሎ ሜትር ሶስተኛ ቦይ(ቴርሸሪ ካናል) በድምሩ 144 ኪሎ ሜትር የቦይና 30 የውሃ ማጠራቀሚያዎች(ፖንዶችን) ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም 60 ኪሎ ሜትር መጋቢ የመንገድ ስራዎች፣ 50 ብሎኮች የያዘ የግድብ አስተዳደርና ለማህበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ ማዕከል ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አርሶ አደሮች ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርቱ፣ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ፣ ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም የቆላማ አካባቢና የአርብቶ አደር ልማትን እውን እንደሚያደርግ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በዘላቂነትም የአካባቢው ማህበረሰብ ምርትን በመጨመር የገቢ አቅሙን እንዲያሳድግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም