ቀጥታ፡

የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓቱን የማዘመን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ጥረት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓቱን ለማዘመን እየተከናወነ ያለውን ተግባር ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባዔ አካሂዷል። 


 

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓትን ለማጠናከር የህግና አሰራር ስርዓቱን የማሻሻል ስራ ተሰርቷል።

ከ4 ሺህ በላይ ተቋማት ውል በተገባለት የመድኃኒት ግዢ ውል መፈፀማቸውን አንስተው በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋናውን ጨምሮ 20 ማዕከሎች በዚሁ መሰረት ስራቸውን እያከናወኑ ነው ብለዋል።

ይህንን ስራ እስከ ጤና ተቋማት ድረስ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የመድኃኒት አቅርቦትን ማዘመን የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት ማቹሪቲ ሌቭል 3 መድረሷ ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም መሆኑን አንስተው ወደ ቀጣይ ደረጃ ለማድረስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ከተቋማት ጋር ውል የተገባለት አቅርቦት ስርዓት በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱን አውስተው በ2017 በጀት ዓመት 68 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓት መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንደገለጹት፤ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማዘመንና የሀገር ወስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የሚያስችል ስራ ተከናውኗል። 

በዚህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ 41 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በጉባኤው የተሳተፉ አካላት የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል የተከናወኑት ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱልሙኒየም አልበሽር አገልግሎቱ ውል የተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት አበረታች ውጤት እየተመዘገበበትና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጎንደር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ይሄይስ ስብሃት በበኩላቸው ያገኙት የእውቅና ሽልማት ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓቱን የሚያዘምኑ ስራዎች መከናወናቸው ለዘርፉ መነቃቃት አስተዋፅኦ ማበርከቱን የተናገሩት ደግሞ የክሊቺ ኢስትሮ ባዮቴክ መድኃኒት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ ናቸው።

በመድረኩ በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ስርዓት የተሻለ ስኬት እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም