በፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን እርካታ ያረጋገጠ የዳኝነት አገልግሎትን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን እርካታ ያረጋገጠ የዳኝነት አገልግሎትን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ በፍርድ ቤቶች በሕዝብ የታመነና የተገልጋዮችን እርካታ ያረጋገጠ የዳኝነት አገልግሎትን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ አስታወቁ።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ ውይይት እና የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም የእውቅና ፕሮግራም መድረክ ተካሄዷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት መንግሥት ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ውጤታማ አገልግሎት የሚሰጡ የፍትህ ተቋማት እንዲፈጠሩ ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም የፍትህ ተደራሽነትን፣ ጥራትንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለተገልጋዩ ከመስጠት አንጻር አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተለይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሰፊ ሥራ መሠራቱ የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ከፍተኛ እመርታ እንዲመዘገብ ማድረጉን አመልክተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተከናወኑ ተግባራት የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ፣ ጥራትንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ይበል የሚያሰኝ ውጤት መገኘቱን ምክትል ስብሳቢው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እና በሕዝብ የታመነ፣ የተገልጋዮችን እርካታ ያረጋገጠ የዳኝነት ተቋም እንዲኖር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አፅነኦት ሰጥተዋል።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር በበኩላቸው በ2017 በጀት ዓመት ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ከዚህ ውስጥም የዳኝነት አገልግሎት ጫናን ለመቀነስ እንዲቻል በርካታ ረዳት ዳኞች እና ሬጅስትራሮች እንዲሾሙ መደረጉን እንዲሁም ለዳኞች፣ ለጉባዔ ተሿሚዎች እና ለሠራተኞች የሙያ ብቃትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ፍርድ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው የተገልጋዮች እርካታ ጥናት በዓለም አቀፍ የፍርድ ቤት መመዘኛዎች ሰባ ስድስት ነጥብ ሶስት በመቶ እርካታ ማስመዝገቡን አንስተው፣ የሕዝብን አመኔታ ያገኙ የዳኝነት ተቋማትን ለመፍጠር በተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።
የፌሰራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አሸነፈች አበበ፥ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ባለፉት ሦስት ወራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት የሕዝቡን እርካታ የሚያረጋግጡ የዳኝነት አገልግሎቶችን ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ውጤታማ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዳኞች፣ ረዳት ዳኞች፣ የመዝገብ ቤት ባለሙያዎችን ጨምሮ ለበርካታ ውጤታማ ሠራተኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።