ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በአሶሳ ከተማ ለህፃናት፣ የእናቶች እና ወጣቶች ክሊኒክ እና የስልጠና ማዕከል ግንባታ ጀመረ

አሶሳ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በአሶሳ ከተማ ለህፃናት፣ የእናቶች እና ወጣቶች ክሊኒክ እና የስልጠና ማዕከል ግንባታ ጀመረ።

በግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ፤ የጤናው ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በአሶሳ የሚገነባው የህፃናት፣ የእናቶች እና ወጣቶች ክሊኒክ እና የስልጠና ማዕከልም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ባለሙያዎች አስፈላጊውን የሙያ ስልጠና እንዲያገኙና ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ በማድረግ በኩል ማዕከሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሂንሰርሙ ባዩ፤ ማህበሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት የሚያሻሽሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአሶሳ ከተማ የሚገነባው ክሊኒክ እና የስልጠና ማዕከል የባለሙያዎችን የፈጠራ እና የምርምር አቅምን የሚደግፍ  እንዲሁም ቀጣይነት  ያለው የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት የጤናው ዘርፍ እንዲሻሻል እያደረገ ላለው ሥራ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም