ታዳጊ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ታዳጊ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ ታዳጊ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ተኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ8ተኛ ጊዜ የዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀንን ''ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው’’ በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለታዳጊ ሴቶች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ታዳጊ ሴቶች በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ታጋላጭ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ የትምህርትና የጤና ጨምሮ አስፈላጊው ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ መሥራት ከሁላችን ይጠበቃል ብለዋል።
ታዳጊ ሴቶች ሙሉ አቅማቸውን ተገንዝበው ለህብረተሰቡ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ይጠበቃል ያሉት ወይዘሮ ሂክማ የሚገጥማቸውን መሰናክሎችን አልፈው በሀገር ግንባታ ውስጥ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማብቃት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ታዳጊ ሴቶች አቅማቸው እንዲጎለብት በትምህርት ያደጉና የተለወጡ እንዲሆኑ የማደረግ ስራ በስፋት መስራቱን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ዙሪያም የፈጠራ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ትምህርትን ለሁሉም ታዳጊ ሴቶች ተደራሽ ማድረግ ላይ የሚስተዋሉ ውስንቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ርብርብ መቀጠሉን አንስተዋል።
በተለይም ታዳጊዎች በመጤ ባህል ሰለባ እንዳይሆኑ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ ስብዕናው የተገነባ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
በታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የግንዛቤ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ከዚሁ ጋር ተያይዘው የወጡ ሕጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።