የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ አረጋገጠ።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አጃይ ቡሻን ፓንዲ ጋር የሁለትዮሽ ትብብሮች ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ አሕመድ እንዳሉት፥ የታዳጊ ሀገራትን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማሳደግ ብሎም ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ በፋይናንስ አቅርቦት ላይ በትብብር መሥራት ይገባል።
ባንኩ ባለፉት ዓመታት ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ለመደገፍ ያደረገውን ጥረትም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ስለምትገነባው ግዙፉ አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትም ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በኢነርጂ ዘርፍ ለሚሠሩ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች የባንኩ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
አጃይ ቡሻን ፓንዲ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና መንግሥት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሰጠውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እና ሀገሪቱ ለዘላቂ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ባንኩ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ እና ባንኩ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በሆኑት ኢነርጂ፣ትራንስፖርት እና ሌሎች ዘርፎች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በሚያስችላቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።