በክልሉ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረጽ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ልማትን ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረጽ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ልማትን ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረጽ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ልማትን ለማፋጠን ከሚዲያው ጋር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ዛሬ ባካሄደው የሴክተር ጉባኤ ላይ የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አሸናፊ ኤልያስ እንደገለጹት፤ በክልሉ የልማት ዕቅዶችን ወደተግባር በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ ውጤት እየተገኘ ነው።
የልማት ግቦች ወደህዝብ ሰርጸው በእኔነት ስሜት እንዲሳተፍባቸውና ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ሚዲያው የጎላ ሚና ሲጫወት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ በማትኮር የህዝብን አንድነት ለማጠናከር፣ የልማት ሥራዎችን ለመፋጠንና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ተግቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም ከሚዲያው ጋር በቅንጅት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን፤ ባለፉት ጊዜያት በዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አተገባበር ላይ ሚዲያን ያሳተፈ ሥራ በመሰራቱ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
ይህም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየተመዘገቡ ላሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አቅም እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
ቢሮው በክልሉ ያሉ የልማት አቅሞች እና ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ እንዲተዋወቁና እንዲለሙ እንዲሁም የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ያዕቆብ እንዳሉት፣ ቢሮው በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን በመጠቀም የዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ ነው።
በተለይ ለክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰጠው ትኩረት በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በመድኩ በክልሉ ከሚዲያው ዘርፍ ጋር በተቀናጀ መንገድ በመስራት እየተመዘገበ ላለው ውጤት አበርቶ ላላቸው አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።