በፕሪሚየር ሊጉ ሲዳማ ቡና ድል ሲቀናው ነጌሌ አርሲ እና አርባምንጭ ከተማ አቻ ተለያይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ሲዳማ ቡና ድል ሲቀናው ነጌሌ አርሲ እና አርባምንጭ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 4 ለ 1 አሸንፏል።
አበባው አጂሶ፣ አስቻለው ሙሴ፣ ተመስገን መንገሻ እና የወልዋሎው ጌታሁን ባፋ በራሱ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሰመረ ሀፍታይ ለወልዋሎ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ብሩክ እንዳለ በጨዋታው ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በኩል በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ብሩክ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ቀይ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች ሆኗል።
አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ እና አርባምንጭ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሀቢብ ከማል ለነጌሌ አርሲ፣ ታምራት እያሱ ለአርባምንጭ ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሸገር ከተማን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።
ድሬዳዋ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ጋር በአሁኑ ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።