ቀጥታ፡

በምርምር ማዕከሉ የቀረበልን የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ በመጠቀም ምርታማነታችንን ለማሳደግ በትጋት እየሰራን ነው -አርሶ አደሮች

ሰቆጣ ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡-  በሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል የቀረበላቸውን የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ  በመቀጠም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በትጋት እየሰሩ መሆኑን  በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የፃግብጅ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በፃግብጅ ወረዳ በምርምር ማዕከሉ የቀረበና  በኩታ ገጠም  የለማ ''ቁንጮ'' የተሰኘ  የጤፍ ዝርያ እንዲሁም የማሽላ ሰብል  ዛሬ  በመስክ ተጎብኝቷል።
 
በወረዳው የአሪሸርወ ቀበሌ አርሶ አደር አወጣ ብርሃኑ በወቅቱ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በምርምር ማዕከሉ የቀረበላቸው ''ቁንጮ'' የተሰኘ የጤፍ ዝርያን በአንድ ሄክታር መሬት አልምተዋል።
 
ካሁን ቀደም በአካባቢ ዝርያ በሄክታር ከ2 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር አውስተው፤ በመኸሩ ወቅት  የተሻሻለው የ''ቁንጮ''  ዝርያን ማዳበሪያ ተጠቅመው  መልማታቸውንና ከዚህም ከ10 ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
 
አሁን ላይ የሰብሉ ቁመና በጥሩ እድገት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤  ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በመንከባከብ ተግተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።  
 
አርሶ አደር ወልደስለሴ ግርማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከማዕከሉ ባገኙት የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ሩብ ሄክታር መሬት ማልማት ችለዋል።
 
አካባቢያችን ዝናብ አጠር በመሆኑ ቀደም ሲል በልፋታቸው ልክ ምርት እንደማያገኙ አስታውሰው፤ በምርምር ማዕከሉ የቀረበው ዝርያ ችግርን በመቋቋም  የተሻለ ምርት እንደሚስጥ ከባለሙያ ትምህርት ወስደው ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በማዕከሉ የቀረበላቸው የ"ቁንጮ" ጤፍ ዝርያ የተሻለ ምርት በማስገኘት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያገዝ ከባለሙያ  ተረድተው በማልማት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሌላው አርሶ አደር ሲሳይ አማረ ናቸው።

 
በማዕከሉ የምጣኔ ሃብትና ግብርና ስርፀት ተመራማሪ  አደመ ምህረቱ እንደገለጹት፤  ማዕከሉ ስነ ምህዳርን መሰረት ያደረጉ የቁንጮ ጤፍና ማሽላን ጨምሮ የየተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ይገኛል።
 
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ዝናብ አጠር በመሆኑ  በአነስተኛ የዝናብ ስርጭት ፈጥነው የሚደርሱ ዝርያዎች ሲቀርቡ እንደቆዩ አውስተው፤   በፃግብጅ ወረዳም ''ቁንጮ'' የተሰኘ የጤፍ ዝርያ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። 
 
በዚህም ማዕከሉ ባደረገው ድጋፍ  በወረዳው አሪሸርዋ ቀበሌ 30 አርሶ አደሮች የተሳተፉበት 10 ሄክታር መሬት ላይ  በኩታ ገጠም ዝርያውን ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
 
ማዕከሉ በአካባቢው የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና እና የስርዓተ ምግብ እጥረት ለማቃለል  የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
ምርምር ማዕከሉ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው።  
 
የምግብ ዋስትናን ችግር ለማቃለል ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አንሰተው፤ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች  ለአርሶ አደሩ የማድረስ ተግባር  በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናገረዋልል።
 
በጉብኝቱ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና በልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም