የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከስዊድን እና ሩሲያ ማዕከላዊ ባንኮች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከስዊድን እና ሩሲያ ማዕከላዊ ባንኮች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከስዊድን እና ሩሲያ ማዕከላዊ ባንኮች ጋር በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰራ አስታወቀ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን አካቷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስብሰባው ጎን ለጎን ከስዊድን እና ሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስዊድን ማዕከላዊ ባንክ ምክትል ገዥ አና ሴም ጋር የቴክኒክ ትብብር እና ተቋማዊ ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
የሞኒተሪ ፖሊሲ ቀረጻ እና ትግበራ፣የፋይናንስ መረጋጋት፣ የብሄራዊ ባንክ የኮሙኒኬሽን ሂደት፣ የክፍያ ስርዓቶች ልማት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የውይይቱ አጀንዳዎች ናቸው።
ሁለቱ ወገኖች በእውቀት ሽግግር፣በተቋማዊ አቅም ግንባታ እና ጥናት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻ ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ በቀጣይ በብሪክስ ጉባኤዎች ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ነው።
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ልማት፣ማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግምጃ ቤት (የሰነዶች ካዝና) ትስስር፣ድንበር ተሻጋሪ ንግድ እና የክፍያ ስርዓትን ማዘመን ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ውይይቶች ላይ ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ብሄራዊ ባንኮች ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ እና በብሪክስ ማዕቀፍ ትብብር መፍጠር የሚችሉባቸውን እድሎችን ለመመልከት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ውይይቶቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣የፖሊሲ ቅንጅትን ለማሳደግ እንዲሁም የባንኩ ሪፎርሞች በማዕከላዊ ባንክ እና የፋይናንስ አስተዳደር ያሉ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።