ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እያንሰራራ ያለውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

ደሴ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እያንሰራራ ያለውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ኢንቨስትመንትና አምራች ኢንዱስትሪውን የሀገሪቱን የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን የማሳደግና አዳዲስ ባለሃብቶችን መሳብ መቻሉን አንስተዋል።

በዚህም ተኪና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን በጥራት፣ በዓይነትና በብዛት በማምረት እንዲሁም ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት መመረቱን ጠቅሰው ዘንድሮም ከ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እያንሰራራ ያለውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የብድርና የቦታ አቅርቦቶችን በማፋጠን ዘርፉ እንዲነቃቃ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ከ4 ሺህ 200 በላይ ባለሃብቶችን በመሳብ ከ655 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ ክልሉ ለመሳብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅንቄ ዘርፉን ከማነቃቃቱ ባለፈ ተኪ ምርት እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።

በከተማው 127 በማምረት ላይ እና 110 ደግሞ በግንባታ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም