ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሸገር ከተማ ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ሸገር፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተገልጋዮች ተናገሩ።

በሸገር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ከተመዘገቡት ከ11ሺህ 224 ተገልጋዮች አብዛኞቹ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን እንደገለጹም ተመላክቷል።

ከተጠቃሚዎቹ መካከል በአስተዳደሩ የፉሪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሁዳ አብዱልከሪም፤ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ እያገኙት ያለው አገልግሎት በእጅጉ መሻሻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት አገልግሎት ለማግኘት ውጣ ውረድ ብሎም ላልተገባ ወጪ ሲዳረጉ እንደነበር አውስተው፤ አሁን ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈልጉትን አገልግሎት በማግኘት ምቹ ሁኔታ አንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በነበረው አገልግሎት ፋይል የመጥፋት አጋጣሚና ሌሎችም ችግሮች እንደነበር በማስታወስ አስተያየት የሰጡት ደግሞ ከገላን ክፍለ ከተማ የመጡ አቶ ወርቅነህ በንቲ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎቹ መልካም ስነምግባር በመላበስ ከአስር ደቂቃ በታች ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እንደሚያስተናግዱና በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ተገልጋይ ከኩራጅዳ ክፍለ ከተማ የመጡት አቶ ሀብታሙ ጆቴ፤ በከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ከ15 ደቂቃ ባነሰ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኦፕሬሽን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ጆብር እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በከተማው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተበታተነና በተራራቀ መልኩ የሚያካሄዱት አሰራር በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና የመረጃ ስርዓቱ ያልተሟላ ነበረ ።

አገልግሎቱን ለማሻሻል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማስጀመር የሚያስፈልጉትን ቴክኖሎጂና የሰው ሃይል በማሟላት ለማሕበረሰቡ ተደራሽ፤ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ይህ አሰራር ከተጀመረ በሶስት ወራት ውስጥም ከተመዘገቡት ከ11ሺ224 ሰዎች ውስጥ አስር ሺህ ሰዎች አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ አገልግሎቱን የበለጠ በማስፋፋት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ለባለሙያው የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ተገልጋዮች የሚጠበቅባቸውን አሟልተው እንዲገኙ ግንዛቤ ከመስጠት ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መመቻቸቱን አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ከሸገር ከተማ በተጨማሪ በቢሾፍቱ፤ አዳማ፤ ሻሸመኔና ጅማ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም