እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠች - ኢዜአ አማርኛ
እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠች

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡- እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሥራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋገጠች።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ልማት እና አፍሪካ ሚኒስትር ዴዔታ ባሮነስ ጄኒ ቻፕማን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ዛሬ በሚጠናቀቀው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የተካሄደ ነው።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
በውይይታቸውም፥ የኢትዮጵያና እንግሊዝን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች በይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
እንግሊዝ በጤና፣ትምህርት፣ኢነርጂ፣ማኑፋክቸሪንግ፣የገቢ አሰባሰብን ለማዘመን የሚያግዙ ቴክኒካል ድጋፎችን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች እያደረገች ያለውን ድጋፍ በይበልጥ እንድታሳድግ አቶ አሕመድ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ያደነቁት ባሮነስ ቻፕማን በበኩላቸው፤እንግሊዝ የኢትዮጵያን የልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ለሚያሳልጡ ተግባራት ድጋፏን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።