ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማር ምርት ለምጣኔ ሃብት እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየተደረገ ነው

ቦንጋ/ባሕር ዳር ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡-በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማር ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት ለምጣኔ ሃብት እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። 

ይህንን ሀብት  ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ጋር በማስተሳሰርና የአናቢዎችን አቅም በማጎልበት የማር ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት ለምጣኔ ሃብት እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየተደረገ ነው።  

የንብ እርባታ በስፋት ከሚካሄድባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የአማራ ክልሎች  ይገኙበታል። 

በሁለቱ ክልሎች በተያዘው የበጀት ዓመት ከ113 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ የማር ምርት ለገበያ ለማቅብ ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን ክልሎቹ አስታውቀዋል።  

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ እንዳመለከተው፤ በማር ምርት የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያመጡ ናቸው። 

በቢሮው የእንሳሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታመነ በቀለ፤  በክልሉ የማር ምርትን ለማስፋት ከሌማት ትሩፋት ጋር በማያያዝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ዘመናዊና ባህላዊ  የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ ከማሰራጨት ባለፈ የአመራረት ዘዴና ሌሎች ስልጠናዎች ጨምሮ በየደረጃው የተጠናከር ድጋፍ  እየተደረገ ነው ብለዋል። 

በዚህም ምርታማነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤  በዘርፉ የተሳተፉ አካላትም ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።

ባለፈው የበጀት ዓመት በክልሉ 71 ሺህ ቶን ማር መመረቱን ያነሱት አቶ ታመነ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ80 ሺህ ቶን በላይ ማር በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

በክልሉ በዘርፉ በመሰማራት ተጠቃሚ እየሆኑ ካሉት መካከል የካፋ ጫካ ማርና ቅመማቅመም ልማት ሕብረት ሥራ ዩኒዬን  አንዱ ነው።

የዩኒዬኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ማሞ እንደተናገሩት፤ የማር ምርትን በማቀነባበርና እሴት ጨምሮ ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የአባል አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል።

ዩኒዬኑ ከ8 ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው 32 ማህበራትን ማቀፉንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማር ምርትን ለማሳደግ መንግስት ዘርፉን ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተሳሰር የሰጠው ትኩረትና ድጋፍ ውጤታማ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ከ33 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ የማር ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና አሣ ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

‎‎‎በቢሮው የንብና ሀር ልማት ባለሙያ አቶ መሀመድ ጌታሁን ለኢዜአ እንዳሉት፤ አርሶ አደሩንና ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በስፋት በማሳተፍና ተጨማሪ ሃብት በመፍጠር እንዲጠቀሙ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም በንብ ማነብ የተሰማሩ  አናቢዎች ካላቸው  ዘመናዊ፣ ሽግግርና ባህላዊ ቀፎዎች  33 ሺህ 333 ቶን ጥራቱን የጠበቀ የማር ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ በተደረገ እንቅስቃሴ 2 ሺህ 498 ቶን የማር ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ ጥቅምትና ህዳር ዋና የማር ማምረቻ ወቅት በመሆኑ ቀሪውን ምርት ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ጥራት ያለው የማር ምርትን ለአካባቢና አገር አቀፍ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱንም አብራርተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳዬ የምድርዓለም ፤  የንብ ማነብ ስራን በዘመናዊ ቀፎ ማከናወን ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ካሏቸው 110 ዘመናዊ፣ የሽግግርና ባህላዊ ቀፎዎች ከ700 ኩንታል ያላነሰ የማር ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። 

በ210 ዘመናዊ፣ ባህላዊና የሽግግር ቀፎዎች የንብ ማነብ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ አቶ ስለሺ አረጋ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ያመረቱትን ማር  በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮመረጃ እንደሚያመለክተው፤ በክልሉ ባለፈው ዓመት 29 ሺህ 100 ቶን የማር ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ፤ አብዛኛው ምርትም ለገበያ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም