የጤና መድህን አገልግሎት በመደጋጋፍ መርህ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎት በመደጋጋፍ መርህ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል

ሰመራ/ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡-ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በመደጋጋፍ መርህ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለጸ።
በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሠመራ ቅርንጫፍ ክልላዊ ቋት ምስረታ እና አቅምን መሠረት ያደረገ መዋጮ ማስተግበሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርህግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም እንዳሉት ዜጎችን ከድንገተኛ የሕክምና ወጪ በመታደግ አምራች እና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
ለዚህም እንደሀገር የተተገበረው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ አገልግሎቱ በመደጋገፍ መርህ በተለይ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በ2003 ዓ.ም በአራት ክልሎች በ13 ወረዳዎች መጀመሩን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በ1ሺህ 195 ወረዳዎች እና በሁሉም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች 63 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዜጎች መካከል መደጋገፍን መሰረት ባደረገ መልኩ የተሻለ መዋጮ መሰብሰብ እንዲቻልና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የገቢን መጠን መሠረት ያደረገ መዋጮ ማስፈለጉንም ተናግረዋል።
እንደ አገር የዜጎችን የመክፈል አቅም መሰረት ያደረጉ የአከፋፈል ሥርአት የመዘርጋት ጅማሬዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ለእዚህም በ2017 በጀት ዓመት 40 ቋቶችን ለማቋቋም መቻሉን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በበኩላቸው በክልሉ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 157 ሺህ ደርሷል፣ በቀጣይም የመክፈል አቅምን መሠረት ያደረገ ክልላዊ ቋት እንዲጎለብት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሰመራ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኢድሪስ በበኩላቸው አገልግሎቱ ህብረተሰብን ማዕከል ያደረገና መደበኛ ገቢ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረጉን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ዜና አገልግሎቱ በሲዳማ ክልል ፍትሐዊና ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ ናቸው።
ኃላፊዋ በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎትን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ወቅት እንደገለጹት የጤና መድህን አገልግሎቱን ለማስፋት በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በትኩረት በመሰራቱ የአገልግሎቱ ተደራሽነት እያደገ መጥቷል።
ለዚህም በ2013 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን መጠቀም ካለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሆኑት 18 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ በ2017 ዓ.ም ሽፋኑ አድጎ 72 በመቶ መድረሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግልቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ኃላፊዋ፣ በተያዘው ዓመትም 680 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።
የአዲስ አባላት ምዝገባና የነባር እድሳት ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ለማከናወን ዝግጅት ተደርጎ ወደተግባር መገባቱንም አመልክተዋል።
ባለፈው ዓመት በውስን መዋቅሮች ላይ ተጀምሮ የነበረው የገቢ መጠንን መሠረት ያደረገ የአባላት ዓመታዊ ክፍያ ዘንድሮ በሁሉም የክልሉ ወረዳና ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈቱ መምጣታቸውን የገለጹት ዶክተር ሠላማዊት ፣ ከመድሀኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረውን ችግር ለመፍታት ቀደም ሲል በክልሉ አንድ ብቻ የነበረውን የህዝብ መድኃኒት ቤት በአሁኑ ወቅት ወደ 26 ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች ላይ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሻሻል መደረጉን ነው የገለጹት።
የጤና ተቋማትን በተሻለ መንገድ ዝግጁ ለማድረግም ለሚሰጡት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ግምታዊ ቅድመ ክፍያ የሚሰጥበት ሥርዐት መዘርጋቱን አስታውቀዋል።