ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ጨምሮ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅሟን የማስጠበቅ ስትራቴጂክ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ጨምሮ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅሟን የማስጠበቅ ስትራቴጂክ ጉዳይ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣በመከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር "የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፣የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ" በሚል ዐቢይ ርዕስ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፥የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ሳይኖራት የህዝቦቿን ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ጨምሮ በቀጣናው የባሕር በር እንዲኖራት ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ጂኦ ስትራቴጂክ ሚናው የላቀ እንደሆነ አስረድተዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር)፤ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የኃይል ሚዛንን ለማስጠበቅ የዓባይ ወንዝና ቀይ ባሕር ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ፣ደኅንነትና ብልፅግና በቀጥታ ከሁለቱ ውሃዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቀድሞ የባሕር ኃይል ማህበር ሊቀ መንበር ሌተናል ሃለፎም መለሰ፤ በቀይ ባሕር ጉዳይ እርሳቸውና የትግል አጋሮቻቸው በርካታ ዋጋ መክፈላቸውን በቁጭት አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የውስጥ ክፍፍልና ውጫዊ ተጽዕኖ የታሪኳ አካል ከሆነው የቀይ ባሕር ባለቤትነት በግፍ እንድትርቅ መደረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በብሔራዊ አጀንዳነት ቀርቦ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የሚደረገው ጥረትም በኢትዮጵያውያን አንድነት ምላሽ እንደሚያገኝ ተናግረዋል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ኮሞዶር ተገኝ ለታ፣ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ ዑስማን፣ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም