ቀጥታ፡

የልህቀት ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚቆም ሚዲያ እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተላበሰ ጋዜጠኛ ለመፍጠር ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡- የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚቆም ሚዲያ እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተላበሰ ጋዜጠኛ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ለሀገር ግንባታ፣ ለዜጎች የመረጃ ተደራሽነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንዲኖረው የዓለምን ነባረዊ ሁኔታ የዋጀ የዘርፉ ባለሙያ እና ቴክኖሎጂ መታጠቅ አለባቸው፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ዘርፉ የሚጠይቀውን ሙያዊ ሥነ ምግባር ተላብሰው ለሀገር ግንባታና ለዜጎች ተደራሽነት በነፃነት መስራት የሚችሉባቸው የህግና የአሰራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡

በቅርቡም የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ዕውቀትና ክህሎት በምርምር፣ በማማከርና ስልጠና ማሳደግ የሚያስችል የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ሥራ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በ25 ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርቱን መስጠታቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሆኖም አብዛኞቹ የጋዜጠኝነት ምሩቃን የንድፈ ሃሳብ እንጂ የተግባር ዕውቀትና ክህሎት እንደሚጎድላቸው ለይተናል ብለዋል፡፡

ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሀሳቡን ተረድቶ ትንታኔ መስጠትና ማብራራት ቢሆንም ክፍተት ይታያል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሥራ ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በየጊዜው መዘመን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ውስን ዓላማን ብቻ ለማስፈፀም እንደነበር ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ጋዜጠኝነት ትፈልጋለች የሚለውን መመለስ የሚያስችል የተቀናጀ ስልጠና አልነበረም ብለዋል፡፡

ጋዜጠኝነት ከዓለም ነባራዊ አውድ ጋር የተጣጣመ ቀጣይነት ያለው ዝማኔ ይፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከልን ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን የሚመስል ዘመኑን የዋጀ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኝነት ሙያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ግቡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ለሀገር ግንባታ የሚቆም፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚተጋ የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኛ ማፍራት መሆኑን አንሰተዋል፡፡

በዚህም የልህቀት ማዕከሉ በብቁ የሰው ሀይል እና በቴክኖሎጂ የተሟላ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ጋዜጠኛውን ብቻ ሳይሆን መገናኛ ብዙኃንን ጭምር እንዲያልቅ እንፈልጋለን ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጥናትና ምርምር፣ ስልጠናና በማማከር ሀገር በቀል እሳቤዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ ጋዜጠኝነት ከጥቅል ወደ ልዩ ዘጋቢነት እየተቀየረ መሆኑን በማስታወስ፤ ጋዜጠኞችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በምርጫ፣ ውሃ፣ ፋይናንስ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ አቬሽን ጋዜጠኝነትና መሰል ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማሰልጠንና በማብቃት የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የምርጫ ጋዜጠኝነት ስልጠና በቅርቡ እንዲሚጀምር በመጥቀስ፤ ከስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ 32 ፕሮፌሰሮች 11 የሥልጠና ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሶስት ወራት በሚሰጠው የምርጫ ጋዜጠኝነት ሥልጠና የተዘጋጁ ሰነዶች የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ፣ ሚዲያና ዲሞክራሲ፣ ሚዲያና ብሔራዊ ጥቅም፣ ምርጫና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ልምድ፣ እንዲሁም ሚዲያ ማህበረሰብና ባህል የሚሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም