የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትን ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትን ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል

ጅማ ፤ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፡-የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትን ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር "የሳይበር ደህንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት" በሚል መሪቃል በጅማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የሳይበር ደህንነት ወርን በማስመልከት በተዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን መድረኩም ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ተመላክቷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን ለማስፋፋት ትኩረት ከመስጠት ባለፈ በሳይበር ደህንነት ላይ ጠንካራ ሥራ እየተሰራ ነው።
ተቋማቱም የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነታቸውን በመቀነስ አስተማማኝ እና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ትኩረት መሰጠቱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የሁልግዜም ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሳይበር ደህንነትን ወርም ይህን እውን ለማድረግና የሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በማለም እንደሚከበር አክለዋል።
በተለይም የስማርት ከተማን በመገንባት ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ የዲጂታል አገልግሎት ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ነው የገለጹት።
ለተግባራዊነቱም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትን ለማጠናከርና የስማርት ከተሞችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጅማ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዋሴ ግርማ በበኩላቸው እንዳሉት በጅማ ከተማ ዲጂታል አገልግሎቶችን በመተግበር ስማርት ከተማ ለመገንባት እየተሰራ ነው።
ለእዚህም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር በከተማዋ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ተቋማት የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል።