ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በመምከር ለችግሮች ዘላቂ መፈትሄ ለመሻት የሁላችንም ጥረት፣ ትብብርና ተሳትፎ ያስፈልጋል-ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ሆሳዕና፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በመምከር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት የሁላችንም ጥረት፣ትብብርና ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሆሳዕና ከተማ "የሴቶች፤የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መምከር ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የወደፊት እጣ ፋንታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፥ ይህንን እድል መጠቀም ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በዚህ ሂደት በተለይም የሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ መሰል የውይይት መድረኮች በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት አለብን በማለት አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በመምከር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት የሁላችንም ጥረት፣ ትብብርና ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲ ምክር ቤት ተወካዮች፣የኃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም