ለሀገራዊ ጉዳይ በጋራ በመቆም ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምንዘጋጅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን-ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ጉዳይ በጋራ በመቆም ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምንዘጋጅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን-ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን

ወላይታ ሶዶ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ):-ለሀገራዊ ጉዳይ በጋራ በመቆም ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምንዘጋጅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በወላይታ ሶዶ ከተማ "የሴቶች፤ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን፥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ተቋማትን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የሚበጁና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ሃሳቦች የተነሱባቸው በርካታ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በውጭ አገራትም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ እና አጀንዳ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን አንስተው፥ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችሉ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
ለሀገራዊ ጉዳይ በህብረት በመቆም ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምንዘጋጅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ኮሚሽነሯ፥ በዚህ ሂደት በተለይም የሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች እገዛና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው መድረክም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።