ቀጥታ፡

ጣና ፎረም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለሚለው መርህ ተግባራዊነት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ጣና ፎረም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለሚለው መርህ ተግባራዊነት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን 11ኛው ጣና ፎረምን ለማካሄድ በተደረጉ ዝግጅቶች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

11ኛው ጣና ፎረም ከጥቅምት 14 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድም ተገልጿል።


 

ፎረሙ "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እና ባህር ዳር ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

በፎረሙ ላይ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በመገኘት በአፍሪካ የደህንነት ችግሮችና አፍሪካዊ መፍትሔዎች ዙሪያ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ተገልጿል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ 11ኛው የጣና ፎረም በከፍተኛ ደረጃ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም በርካታ ለውጦች እያስተናገደች መሆኑን ገልጸው፤ አፍሪካ ''በምን መልኩ ዕድሎችን ትጠቀማለች? እንዴትስ አትራፊ መሆን ትችላለች?'' የሚለው ርዕሰ ጉዳይ ዋነኛ የፎረሙ ማጠንጠኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፎረሙ በመሪዎችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ምክክር የሚደረግበት መርሃ ግብር ያካተተ መሆኑን ገልጸው፤ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዩ መልዕክተኞች እንደሚወያዩም አብራርተዋል።

ጣና ፎረም ለሌሎች አህጉራዊ መድረኮችም እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በፎረሙ እንደመፍትሄ የሚነሱ ሀሳቦች ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህን የተከተለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ በአፍሪካ አገራት መካከል የጋራ አጀንዳዎች በመቅረጽና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሜርሲ ፍቃዱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፤ የጣና ፎረም የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች እየፈለቁበት መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከአፍሪካ ውጪም ተሳታፊዎችን የሚጋብዝ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም አጋርነት እንዲጠናከር ትልቅ ሚን እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም