ቀጥታ፡

ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት-ኮሚሽኑ

ቦንጋ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ''የሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኛች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር'' በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶች በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በሰላም እጦት በዋናነት ተጎጂዎች ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በመሆናቸው ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ አደረጃጀቶች የታቀፉ ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ለልዩነትና አለመግባባት መንስኤዎች ናቸው ያሏቸውንና ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው ይገባል የሚሏቸውን የአጀንዳ ሀሳቦች በማደራጀት ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡

ስለ ኮሚሽኑና የምክክሩ ሂደት ህዝቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጾም በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዛሬ የውይይት መድረክ ዓላማም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተወጣጡ ወጣቶች፣ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ለቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራ ምክረ ሀሳብ እንዲሰጡና ምክክር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከክልሉ የተወጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች እየተሳተፉ ሲሆን የሀገራዊ ምክክር ምንነትና የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ሚናን የሚያሳይ ሰነድም ለውይይት ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም