የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ለማምጣት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ለማምጣት አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባዔው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራልና ክልሎች የጤናው ዘርፍ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ለማጠናከር የሚያስችል የአዋጅ፣ አሰራር ስርዓት ማሻሻያ ተደርጓል።
የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉንም አስረድተዋል።
ከመንግስትና አጋር አካላት ጋር የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
ከተቋማት ጋር ውል የተገባለት አቅርቦት ስርዓት በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 68 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ መድኃኒትና ሕክምና ግብዓት መሰራጨቱን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከ22 ሺህ በላይ የመንግስት ተቋማት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማዘመንና የሀገር ወስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የሚያስችል ስራ ተከናውኗል።
በዚህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ 41 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።