ቀጥታ፡

የ"መልካ ባሮ"ኢሬቻ በዓል በጋምቤላ ከተማ ተከበረ

ጋምቤላ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦የ"መልካ ባሮ" ኢሬቻ በዓል በጋምቤላ ከተማ የህዝቦችን አብሮነትና ትስስር በሚያጠናክር መልኩ ተከብሯል።

"ኢሬቻ ለወንድማማችነትና ለሀገር ማንሰራራት"በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የተገኙት ታዳሚዎች በዓሉ የህዝብን ማህበራዊ መስተጋብር እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።


 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አባገዳ ሀይሉ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ ‎ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ የክረምት መውጣትና የጸደይ ወቅት መግባት ተከትሎ ተሰባስቦ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓል ነው።

በዓሉ በአብሮነትና በይቅርታ በአደባባይ የሚከበር ህዝባዊ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን በዓል መሆኑን የመልካ ባሮ ኢሬቻ ማሳያ ነው ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ኡዶል አጉዋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥የኦሮሞ ህዝብ ባህሉንና ወጉን አስጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከሚያስችሉት ባህላዊ ሀብቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል።


 

በዓሉ በጋምቤላ ከተማ በድምቀት መከበሩ የኦሮሚያና የጋምቤላ ህዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ገልፀዋል።

የአብሮነትና የወንድማማችነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መከበሩ የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነትን ያጠናክራል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ ቢቂልቱ ቢቂላ ናቸው።


 

ኢሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመቻቻል፣ በመከባበር እና በመፈቃቀር በጋራ የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ከሚያሳዩባቸው ሁነቶች መሆኑንም ተናግረዋል።

ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በተከበረው የመልካ ባሮ ኢሬቻ በዓል ላይ አባገዳዎች፣ሃደ ሲንቄዎች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም