በዞኑ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፡- በአዊ ብሔረሰብ ዞን በነባርና አዲስ የመስኖ አውታሮች 42ሺህ 123 ሄክታር መሬት ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በበጋው ከሚለማው ከዚሁ መሬት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ቤዛዊት ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም በዘንድሮ የበጋ ወቅት አርሶ አደሮችን በመደገፍ 42 ሺህ 123 ሄክታር መሬት በነባርና በአዲስ መስኖ ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ 28ሺህ ሄክታሩ የስንዴ ልማት የሚሸፈን መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ዘር ስራ ለመግባት አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም የማደራጀት፣ የመሬት ልየታና የእርሻ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በስንዴ ከሚለማውም ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።
ቀሪው መሬት የሚለማው ሽንኩርትን ጨምሮ በተለያየ አትክልት መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከሁለት ሺህ 500 በላይ ሄክታር በማረስና በማለሳለስ ለዘር ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱን በኩታ ገጠም አሰራርን በመጠቀምና ግብአትን በወቅቱ በማቅረብ ከዚህ ቀደም በሄክታር 37 ኩንታል የነበረው ምርታማነት ወደ 41 ኩንታል ለማሳደግ ግብ መያዙን አንስተዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ20 ሽህ 700 በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ብቻ በማልማት ከ768 ሸህ ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።