ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ያገኛል።

ሊጉ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን በእያንዳንዱ ምድብ 10 ክለቦች ይገኛሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ፋሲል ከነማ ስሑል ሽሬ፣ መቻል፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ ፣ሃዋሳ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንድርታ፣ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ አንድ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው።

በምድብ ሁለት ነገሌ አርሲ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ሸገር ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተደልድለዋል። 

የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዘጠኝ ሳምንታት ውድድር በአዲስ አበባ እና ሃዋሳ ከተሞች ይካሄዳሉ።

በዚሁ መሰረት የመጀመሪያ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት፣ ነገሌ አርሲ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት እና ድሬደዋ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

በድሬደዋ ሊደረጉ የነበሩ የሊጉ የመጀመሪያ ዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎች ከተማዋ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆኗን ማሳወቋን ተከትሎ ምክንያት ወደ ሃዋሳ መዘዋወራቸው የሚታወስ ነው። 

የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። 

20ዎቹ ክለቦች በ38 የውድድር ሳምንታት 380 ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም