ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና መርሀግብሮች ከተረጂነት ወደምርታማነት ለመሻገር የሚደረገውን ጥረት እያገዙ ነው

አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ):-በአርባ ምንጭ ከተማ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና መርሀግብሮች ከተረጂነት ወደምርታማነት ለመሻገር የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን የከተማው ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ መተኪያ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና መርሀግብሮችን ማስጀመራቸውን ተከትሎ በከተማው ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ ነው።


 

በልማቱም የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎችና የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በስፋት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፣ በመርሀግብሮቹ ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሀግብሮቹ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የአመጋገብ ሥርአትን ከመቀየር ባለፈ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ ከተረጂነት ወደምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በወተት ላሞችና  በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ እንዲሁም በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

በዘርፉ የተሠማሩ አካላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአስተዳደሩ በኩል የመስሪያ ቦታና የገንዘብ ብድር አገልግሎት እንዲሁም የገበያ ትስስርና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አቶ መተኪያ አስረድተዋል።

በከተማው በሌማት ትሩፋት ትግበራ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል "ነህሚያ የእንስሳት እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ ህዝቅኤል ኦሎባ፣ ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የቦታና የገንዘብ ብድር ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ማህበሩ ወደስራ መግባቱን ተናግሯል፡፡

በእንስሳት እርባታ ሥራ ውጤታማ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የወተት ምርታቸውን ለተጠቃሚው ማቅረብ መጀመራቸውን ገልጿል፡፡


 

የ"አዲስ ዓለም" የዕንቁላል ዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ታምራት እንዳለ በበኩሉ እንደገለጸው በ2016 በማህበር ተደራጅተው ከ270 በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል፡፡

ትምህርት ቤቶችም ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በከተማ ግብርና የጓሮ አትክልት በማልማት የውስጥ ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  የከተማው ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መለሰ መንዛ ናቸው።


 

እያንዳንዱ ትምህርት ቤት በከተማ ግብርና ሥራ በዓመት እስከ 700 ሺህ ብር በማግኘት የውስጥ ገቢውን ከማሳደግ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም