ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ምክትል ሰብሳቢው ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የባሕር በር ማግኘት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለና ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ የባሕር በር እንደነበራት አስታውሰው፤ የባህር በሩን ያጣችው በታሪካዊ ጠላቶቿ ሴራና በወቅቱ በነበሩ መሪዎች ቸልተኝነት መሆኑን አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የባሕር በር የሌላቸው ሃገራትን የባሕር በር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎችን ማስቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

ህጉ የባሕር በር የሌላቸው አገራት ዝግ ሆነው መቀጠል እንደሌለባቸውና ባሕሩም ሆነ በባሕሩ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች የጋራ ሃብት እንደሆኑ ያስቀምጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከእነዚህ ህጎች የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥያቄው አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ እና ማንም ሀገር የባሕር በር በማጣት ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ኋላ እንዳይቀር የሚያደርግ ህግ መኖሩን ተናግረዋል።

ህጉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የባሕር በር እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ለህጉ ማስፈጸሚያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዋዛ የድርጊት መርሃ ግብርን አዘጋጅቶ ስራ ላይ ማዋሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ተወዳዳሪና ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡

የምርቶች በስፋት ለገበያ መቅረብ ደግሞ ጥቅሙ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር እንደሚሆን ተናግረዋል።

የባሕር በር ጉዳይ አሁን ላይ ከመንግስት አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን አጀንዳ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም