የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለባቡር መሰረተ ልማት ሥራዎች ትልቅ ዕድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለባቡር መሰረተ ልማት ሥራዎች ትልቅ ዕድል ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለባቡር መሰረተ ልማት ሥራዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ካሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለባቡር መሰረተ ልማት ስራዎች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀስ የባቡር መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት መስጠቷን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ለሚገኙ የባቡር መስመሮችና በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች መስመሮችን ለመዘርጋት የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት እድሎችን እንደሚያሰፋ ጠቁመዋል።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ስምንት መስመሮችን በመዘርጋት የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ታቅዷል።
እነዚህ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን በባቡር መሰረተ ልማት የተሳሰረች እንደምትሆን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአማራጭ ወደቦች ተጠቃሚ እንድትሆን የሚከናወኑ ስራዎችን ለማሳለጥ እንዲቻል ከምርት ስፍራ እስከ ወደብ የሚያስተሳስሩ የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ስለሺ ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ከደረቅ ወደብ ጋር በባቡር መሰረተ ልማት ማስተሳሰር መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚኖሩ የንግድ ቀጣናዎችን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የባቡር ዘርፍ እድገቱን ለማሳለጥ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከደቡብ ኮሪያ ቴክኒካል ድጋፍ ለማግኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚሰሩ የባቡር መሰረተ ልማት ስራዎችን 80 በመቶ የሚሆነውን በራስ አቅም ለመስራት ታቅዶ ክፍሎችን የማደራጀትና የሙከራ ፕሮጀክት ትግበራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ለባቡር አካላትና ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውሉ ምርቶችን ማምረት የተጀመረ ሲሆን፤ በቀጣይም ሙሉውን ባቡር ወደ ማምረት ስራ ለመግባት የማደራጀትና ሌሎች ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።