የሊጉ መሪ አርሰናል ከፉልሃም ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ አርሰናል ከፉልሃም ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በኋላ በስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይመለሳል።
ፉልሃም ከአርሰናል ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የምዕራብ ለንደኑ ፉልሃም በስምንት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በ16 ነጥብ የሊጉ መሪ ነው።
አርሰናል ካሸነፈ ከተከታዩ ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ያደርጋል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን፣ ብራይተን ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ክሪስታል ፓላስ ከቦርንማውዝ፣ በርንሌይ ከሊድስ ዩናይትድ እና ሰንደርላንድ ከዎልቭስ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ቀን 8 ሰዓት ከ30 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከቼልሲ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።