በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የባሌ ዞን የመጀመሪያ ቀን ጉብኝት ያሳየን በድንቅ ተፈጥሮ እና በልማት ሥራ እድገት መካከል ያለውን መስተጋብር ነው ብለዋል።
በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል ሲሉም አክለዋል።
ይኽ እምቅ አቅም በፓርኩ እምብርት ላይ የተገነባው የዲንሾ ሎጅ በቅርቡ ሲጠናቀቅ የበለጠ ይጠናከራል ነው ያሉት።
በአቅራቢያው በመገንባት ላይ ያለውና በቅርቡ የሚጠናቀቀው የሶፍኡመር ሎጅ ቱሪዝምን የኢኮኖሚያችን ቁልፍ መሪ አድርጎ ያስቀመጠው የኢትዮጵያን የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ የሚተገብር ነው ብለዋል።
ሎጁ በሶፍኡመር ዋሻ የጎብኚዎችን ቆይታ ከፍ የሚያደርጉ እና የመዝናኛ አገልግሎት መስጫዎች በሶፍኡመር ዋሻ ልማት ፕሮጀክት እገዛ የሚዘጋጁበት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
በመንገድ መሠረተ ልማት ረገድ የሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መንገድ የማሻሻያ ፕሮጀክት ከፍተኛ አምራች የሆኑትን የምሥራቅ ባሌ እና የባሌ ዞኖችን ምርታቸውን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ነውም ነው ያሉት።
ይኽ መሥመር ተደራሽነትን እና የኢኮኖሚ ተያያዥነትን ብቻ ሳይሆን እንደሶፍኡመር ዋሻ እና የባሌ ተራሮች ወደ መሰሉት ዐበይት የመስኅብ ሥፍራዎች ጉዞን የሚያሳልጡ ናቸው ብለዋል።
ድርብ አስፋልት ንጣፍ ባለው ከፍ ያለ ደረጃ የተገነባው መንገድ 29 ኪሎሜትር የከተማ እና የገጠር መንገድን የሚያካትት ብሎም ከ12 እስከ 140 ሜትር ርዝመት ያላቸው አምስት ድልድዮች የተሠሩበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቀኑን ጉብኝታችንን የወይብ ወንዝ የጎርፍ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክትን በመመልከት አጠናቀናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ለቢይ አሕመድ(ዶ/ር)።
ፕሮጀክቱ በሶፍኡመር ዋሻ የሚጓዘውን የወንዙን የውሃ ፍሰት በመቆጣጠር አመቱን ሙሉ ወደ ዋሻው የሚደረግ ጉዞ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ብሎም የዋሻውን ሥነምኅዳር ለመጠበቅ ታልሞ የተሠራ ነውም ብለዋል።
ሁሉም ሥራዎች ቀጣይነት ላለው ልማት ያለንን ጽኑ አቋም እና ተግባር የሚገልጡ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመልዕክታቸው።