ቀጥታ፡

በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ትብብርና እገዛ የላቀ ትርጉም አለው

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ትብብርና እገዛ የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ያቋቋመውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል መርቀው በይፋ ስራ አስጀምረዋል።


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት የአጋር ድርጅቶች እገዛ ትልቅ ትርጉም አለው።

በመሆኑም ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ የጀመረው የሆስፒታል ግንባታና ዛሬ ያስመረቀው የኩላሊት እጥበት ማዕከል የክልሉ መንግስት በሚያከናውነው የጤና ልማት ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የማዕከሉ አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠው በዛሬው እለት  የ10 ሚሊዮን ብር እና የአምቡላንስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የኩላሊት በሽታን ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ለበሽታው ታማሚዎችም የህክምና ጥራትና አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በመሆኑም ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ያቋቋመው የኩላሊት እጥበት ማዕከል መንግስት የጤናውን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ አገልግሎት የተሟላና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ጤና ሚኒስቴርና የክልሉ ጤና ቢሮ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በ29 ሚሊዮን ብር ያቋቋመውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል ድጋፍ ለሚያደርግላቸው አረጋውያን እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ህሙማን ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎት እንደሚሰጥ የገለጹት ደግሞ የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ናቸው፡፡


 

ማእከሉ  ከሌሎች ህክምና ማዕከላት ባነሰ ክፍያ ከሰኞ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልፀው ህብረተሰቡ የማዕከሉ አባል በመሆን የአገልግሎቱን ቀጣይነት እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት ከጀመሩ አምስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው አቶ ታገሰ ፋንቱ በበኩላቸው የማእከሉ መከፈት ኢኮኖሚያዊ ጫናቸውን እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል፡፡


 

በማዕከሉ መከፈት መደሰታቸውን ገልጸው አገልግሎቱን ለማግኘትም የአባልነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተክሌ ጆምባም ለማዕከሉ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ባለሃብቶችና የተለያዩ ተቋማት፣ እንዲሁም ግለሰቦች የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም