በአፍሪካ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቱን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቱን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ዘላቂና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቱን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት ዛሬ ተጠናቋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) መርሃ ግብሩ፣ በአፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ጥራት ለመጠበቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ያካፈለችበት እና ከሌሎች ልምድ የወሰደችበት ስኬታማ መድረክ እንደነበርም ገልጸዋል።
የአፍሪካ መጻዒ እድል የሚወሰነው በወጣቶች ላይ በምንሰራው ሁሉን አቀፍ የክህሎት ልማት ስራ ልክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ዘላቂና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቱን የፈጠራና የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሰው ሀብት ልማት ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ በቀጣይም ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በማስተሳሰር አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያም የአፍሪካ አገራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ሀብት ለማፍራት በጋራ የሚሰሩበት አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋስፓርድ ዳንያንክምቦና በበኩላቸው፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት የእድገት ማሳለጫ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአፍሪካ አገራት በአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳ መሰረት ቅንጅት በመፍጠር ዘርፉን በማሳደግ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ማፍራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የዛሬ የአፍሪካ ወጣቶች ነገን ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ መምራትና ለውጥ የማምጣት ሃላፊነት እንደተጣለባቸው አንስተው፤በዚህ ሒደት ውስጥ ከጎናቸው እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡
ከኢኳቶሪያል ጊኒ የመጡ የመድረኩ ተሳታፊ ዮላንዳ አሱሙ በበኩላቸው፤ ሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት በርካታ ልምዶችን የተለዋወጥንበት ነበር ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሁለተኛው ክህሎት ሳምንት እጅግ አስተማሪና ትልቅ ግንዛቤ የወሰድንበት ሆኖ አልፏል ያለው ደግሞ ከሴኔጋል የመጣው ወጣት ደቪድ ሞዓድ ነው፡፡