ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የወላጆች ሚና እና ሃላፊነት ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የወላጆች ሚና እና ሃላፊነት ከፍተኛ ነው

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የወላጆች ሚና እና ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጋምቤላ ክልል አዳሪ ትምህርት ቤት እና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በዛሬው እለት አስጀምረዋል።
ሚኒስትሩ መርሃ ግብሩን ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ በራስ ጉበና 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወላጆች እና የትምህርት ማህበረሰብ አካላት የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሩ በመልክታቸውም ሀገር ተረካቢው ትውልድ የተሻለ እንዲሆንና ለሀገሩ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በትምህርት ሂደት ውስጥ ማለፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተለይም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ቤተሰባዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የወላጆች ሚና እና ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ትውልዱ በክህሎትና በስነ- ምግባር ታንፆ ካለደገ ነገ ሀገር በመረከብ ረገድ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ወላጆችና የትምህርት ማህበረሰቡ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
መንግስት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን የትምህርት እድል ተጠቃሚ በማድረግ የትውልድ ግንባታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።