በክልሉ በበጋ መስኖ በአትክልትና ሆርቲካልቸር ልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በበጋ መስኖ በአትክልትና ሆርቲካልቸር ልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

ቦንጋ፣ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመጀመሪያው ዙር የበጋ መስኖ የአትክልትና ሆርቲካልቸር ልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመላከተ።
በክልሉ የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እና የግብርና ግብዓት አውደ ርዕይ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቢሮ የሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገብረ ሚካኤል፣ በክልሉ ያለው ስነ-ምህዳርና የአየር ፀባይ በተለይም ለሆርቲካልቸር ልማት ተስማሚ መሆኑን አንስተዋል።
በአትክልትና ስራስር እንዲሁም በፍራፍሬ ልማት እምቅ አቅም መኖሩን ገልጸው በዚህም በበጋው የመስኖ ልማት ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት የልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በክልሉ በመጀመሪያው ዙር የበጋ መስኖ የአትክልትና ሆርቲካልቸር ልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በዘርፉ ልማት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከ50 ሺህ ሄክታር መሬት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አስታውሰው ዘንድሮ ከዚህ የላቀ ምርት ሊገኝ እንደሚችል አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት በበጋ መስኖ ልማት የመጀመሪያው ዙር ከ55 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወርቁ፤ የሆርቲካልቸር ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የቦንጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አስረስ አስፋው በበኩላቸው፣ በሆርቲካልቸር ልማት በክልሉ እምቅ አቅም ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ሳይሆን ምርታማነቱ ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ምርታማነትን ለማሳደግና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር አውደ ርዕዩ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ሼህ መሐመድ አደም፤ በመንግስት የመስኖ አውታር ከመገንባት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ በመሆኑ በስፋት በማልማት ከፍተኛ ምርት ለማግኘት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በቦንጋ ከተማ በተካሄደው አውደ ርዕይ ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘሮች፣ ችግኞች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን በአቅራቢዎችና በሸማቾች መካከልም የቀጥተኛ ግብይት ዕድል የተፈጠረ መሆኑ ታውቋል።