ቀጥታ፡

የአፍሪካ መጻዒ እድል የሚወሰነው በወጣቶች ላይ በሚሰራ ሁሉን አቀፍ የክህሎት ልማት ስራ ልክ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ መጻዒ እድል የሚወሰነው ወጣቶች ላይ በምንሰራው ሁሉን አቀፍ የክህሎት ልማት ስራ ልክ ነው ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ።

ከጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት ዛሬ ተጠናቋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ መድረኩ በአፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ጥራት ለመጠበቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ያካፈለችበትና ከሌሎች ልምድ የወሰደችበት እንደነበርም ገልጸዋል።


 

የአፍሪካ መጻዒ እድል የሚወሰነው በወጣቶች ላይ በምንሰራው ሁሉን አቀፍ  የክህሎት ልማት ስራ ልክ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአህጉሪቱ በሰው ሀብት ልማት ዘርፍ በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለሰው ሀብት ልማት ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ በቀጣይም ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በማስተሳሰር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያም የአፍሪካ አገራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ሀብት ለማፍራት በጋራ የሚሰሩበት አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም