የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ግብዓት በማሟላት ማጠናከር ይገባል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ግብዓት በማሟላት ማጠናከር ይገባል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ግብዓት በማሟላት ማጠናከር እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚገነቡ የአዳሪና የክልል ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ግንባታዎቹን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ በማድረግና ግብዓት በማሟላት ማጠናከር ይገባል።
ከዚህም ባለፈ የመምህራንን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሞዴልና አዳሪ ትምህርት ቤቶች የመገንባት እንዲሁም የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ረገድ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተከናወኑ ባሉት የለውጥ ስራዎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣቸውንም ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ ዛሬ የተጀመሩትን ጨምሮ እንደ ሀገር 13 ሀገር አቀፍ የአዳሪና 31 የክልል ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን፣ በክልሉ የሚገነባው ሀገር አቀፍ አዳሪ ትምህርት ቤት ለትምህርት ጥራት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ቀደም ሲል ያስጀመረውን ጨምሮ ለክልሉ እያስገነባቸው ያሉት ሞዴል ሁለት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጥራቱ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።