ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የበለጠ የሚያጠናክር ቁልፍ ፕሮጀክት ነው -የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድንበር ተሻጋሪ የኢነርጂ ንግድን ጨምሮ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የበለጠ የሚያጠናክር ቁልፍ ፕሮጀክት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።


 

26ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ከባንኮቹ ዓመታዊ ምክክር ጎን ለጎን ተደርጓል።

በስብሰባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አመራሮች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።

የሶማሊያ የገንዘብ ሚኒስትር ቢሂ ኢማን ኢጌህ እና የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንድያሜ ዲዮፕ ስብስባውን በጋራ መርተውታል።

ሚኒስትሮቹ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሂደትን የገመገሙ ሲሆን በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ውስጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እና ትስስርን የሚያጠናክሩ የፖሊሲ ምላሾች መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች በተለይም የድንበር አቋራጭ ልማት እና የድንበር ተሻጋሪ ልማት ፍኖተ ካርታ ትግበራን አስመልክቶም ውይይት ተደርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በስብስባው ላይ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ ቀጣናዊ ተጠቃሚነቶች የሚያረጋግጡ ኢኒሼቲቮች ያሉበትን ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

በቅርቡ የተመረቀው የህዳሴ ግድብ ድንበር ተሻጋሪ የኢነርጂ ንግድ በማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ ሀገራትን የእርስ በእርስ የንግድ ለውጥ የሚያሳድግና በድንበር አካባቢ ላሉ ማህበረሰቦች አዳዲስ እድሎችን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ትስስር በማጠናከር ያመጣቸውን ለውጦች ያደነቁ ሲሆን ማዕቀፉን የበለጠ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጎልበት መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አጋሮች ለኢኒሼቲቩ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ያላትን ቁርጠኝነት በመግለጽ የልማት አጋሮች ድንበር ተሻጋሪ ልማትን ጨምሮ የኢኒሼቲቩን ዘላቂነት ለማስቀጠል ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ 2019 ማብቂያ በአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስትሮች የተቋቋመ ነው።

በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረትና በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተው ኢኒሼቲቩ ንግድ እና ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከርን ዋነኛ አላማው አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም