ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት ትግበራ የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በማግኘት የወተት ምርት ተጠቃሚነታችንን አሳድጎታል-ነዋሪዎች

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሌማት ትሩፋት ትግበራ የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በማግኘት የወተት ምርት ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገው በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ነዋሪዎች ገለጹ። 

የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻልና የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማስቻሉን አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ 744 ሚሊዮን ሊትር የወተት ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።


 

በክልሉ በእንስሳት እርባታ ከተሰማሩት መካከል በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ የአላቻ ከብት እርባታ ባለቤት ገራድ ተስፋዬ ተፈራ እንደገለፁት፣ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ምርታማነታቸውን እያሳደገው ነው።


 

በዚህም በትግበራው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የወተት ላሞችን በማግኘት የወተት ምርታማነታቸውን ማሳደጉን ተናግረዋል።

የአካባቢን ሥነ ምህዳር የተላመዱ የወተት ከብቶችን በማዳቀል የተጀመረው የዝርያ ማሻሻል ስራው በወተት ምርት የተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ካላቸው ላሞች በቀን 670 ሊትር ወተት ለሆሳዕና ከተማ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው፣  መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል፡፡

በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ዛቶ ሾደራ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ አማረች ወልደሰማያት በበኩላቸው እንዳሉት ፣ መንግሥት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለእንስሳት ዝርያ ማሻሸያ ትኩረት መስጠቱ ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።


 

ከዚህ ቀደም ከሀገረ ሰብ ላሞች የሚገኘው የወተት ምርት ብዙ እንዳልነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ካሏቸው የተሻሻሉ ላሞች በቀን እስከ 100 ሊትር ወተት ለሽያጭ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሚያገኙት ገቢ ልጆችን ማስተማርና የራሳቸውን መኖሪያ ቤት ከመገንባት ባለፈ ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ እየመሩ እንዳሉ ጠቅሰው፣ ተጠቃሚነታቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ተረፈ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በክልሉ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በትግበራው የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል በወተት ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ የተቀረፁ ሀገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮችን በመተግበር በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 


 

በተለይ የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ለተሻሻለ መኖ ዝግጅት፣ ለእንስሳትን ጤና አጠባበቅና አያያዝ ትኩረት መሰጠቱንና በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የሌማት ትሩፋት ትግበራ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱንና በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ህይወትም ተጨባጭ ለውጥ እያሳዩ መምጣቱን ገልጸዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በክልሉ ዓመታዊ የወተት ምርት 321 ሚሊዮን ሊትር የነበረ ሲሆን የሌማት ትሩፋት ትግበራን ተከትሎ በተያዘው ዓመት 744 ሚሊዮን ሊትር ወተት ለማምረት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በክልሉ ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራ በተሰጠው ትኩረት አርሶ አደሩ በቀን በአማካኝ 38 ሊትር ወተት እንዲያገኝ ማስቻሉን የጠቀሱት አቶ ኢያሱ፣ ይህም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አሳድጎታል ብለዋል።

በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አጠናክሮ በማስቀጠል ክልሉን በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

ክልሉ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም በበጀት ዓመቱ 243 ሺህ ላሞችን በማዳቀል 123 ሺህ ጥጆች ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ኢያሱ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም