ቀጥታ፡

በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ሁሉ ምቹና ቀልጣፋ የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል- ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹና ቀልጣፋ የአሰራር ስርአት መዘርጋቱን የጋምቤላ ክልል ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

"የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እድሎች፤ ለአምራች ዘርፍ ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፤ በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪን ጨምሮ በብዙ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችሉ እምቅ ጸጋዎች እንዳሉ ገልጸዋል።


 

በተለይም ለግብርና እና የማዕድን ልማት፤ ለእንስሳት እርባታና የንብ ማነብ ስራ ያልተነካ መሬትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመኖሩ በዘርፉ የሚሰማሩ ሁሉ አትራፊና ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በመሆኑም በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹና ቀልጣፋ የአሰራር ስርአት የተዘረጋ በመሆኑ ባለሃብቶች በክልሉ እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ስኬታማነት ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።


 

የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማስፋትና ምርታማነቱን ለማሳደግ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን ስኬት በማላቅ አምራችነትን ማበረታታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። 

የዘርፉን ልማት ለማሳደግ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለላቀ ስኬትና ውጤታማነት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ በማሳደግ ለሀገር እድገትና ማንሰራራት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማስፋትና የማምረት አቅሙን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደረግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም