ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል እየተሰራ ነው

አዳማ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን  የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ።

20ኛው የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ''ስፖርት ለሀገር ማንሰራራት'' በሚል መሪ ሃሳብ የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሄዷል።


 

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት በክልሉ  የህዝቡን የልማት ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የስፖርት መሰረተ ልማት ዝርጋታ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት በዚህ ረገድ ትልቅ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በበርካታ አካባቢዎች የወጣቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የስፖርት አካዳሚዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።


 

የተሰሩት ስራዎችም የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያግዙ ከመሆናቸውም በላይ ወጣቶች በመልካም ስብዕና እንዲታነጹ እና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ እድል እየፈጠሩ መሆኑን አውስተዋል።

እስካሁን የተከናወኑ የስፖርት መሰረተ ልማት ስራዎች አበረታች ቢሆኑም አሁንም ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ አለበት ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ በበኩላቸው ክልሉ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ስፖርተኞችን ለሀገር ያበረከተ ነው ብለዋል።


 

የክልሉ የስፖርት ዘርፍ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በቀጣይም አዳዲስ የአትሌቲክስ ክለቦችን ለማደራጀትና ለማጠናከር የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች እንደሚተገበሩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም